ኢትዮጵያ፡ ለአንድ ሳምንት ‘የዲጂታል ጦር አውርድ’ ያወጁት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን

የዛሬ ዓመት ግድም ነው። ዶ/ር ዓለማየሁ አስፋው ገብረየስ ከወዳጃቸው አንድ የስልክ ጥሪ ይደርሳቸዋል። ወዳጃቸውም ዶ/ር ዮናስ ይባላል። እንደሳቸው ሐኪም ናቸው።

እረ ባክህ አንተ ሰው፣ ይሄን የሐኪሞች ማኅበርን መስመር እናሲዘው፣ ምነው ዝም አልክ?” የሚል የወዳጅ ጥሪና ወቀሳ ያደርሷቸዋል።

ዶ/ር ዓለማየሁ በስኮትላንድ ከፍተኛ የካንሰር ስፔሻሊስት ናቸው። በታላቋ ብሪታኒያ የኢትዮጵያዊያን ሐኪሞች ማኅበር አባልም ናቸው። ወቀሳውም ከዚሁ ማኅበር ጋር የተያያዘ መሆኑ ነበር።

ያ ወቅት ግን ዶ/ር ዓለማየሁ ስለሙያ ማኅበር የሚያስቡበት ጊዜ አልነበረም። ቆዝመዋል። አዝነዋል። ተረብሸዋል። ግራ ገብቷቸዋል። እትብታቸው ከተቀበረባት ከአገራቸው ኢትዮጵያ የሚመጡ ዜናዎች በሙሉ የሚረብሹ ነበሩ። ልክ የዛሬ ዓመት ኦክቶበር ወር አካባቢ መሆኑ ነው ይሄ።

እርግጥ ነው በዚያን ጊዜ ከኢትዮጵያ በተለይም ከኦሮሚያ አካባቢ የሚወጡ ዜናዎች ልብ የሚሰብሩ ነበሩ።

“ምን የሐኪም ማኅበር እናጠናክር ትለኛለህ፣ አገር እንዲህ እየታመሰች…” ይሉታል፣ ወዳጃቸውን፣ ዶ/ር ዮናስን፣ ከቁዘማው ሳይወጡ። ዶ/ር ዮናስም ሐዘን ገባቸው። ሐሳብ አወጡ አወረዱ።

“ታዲያ የኛ ማዘን ምን ሊፈይድ ነው፤ አንድ ነገር እናድርግ፣ ሐሳብ እናዋጣ። ነገ ምን ይመጣ ይሆን በሚል ዳር ቆሞ የሚያይ በቂ ሕዝብ አለ። እኛ እዚያ ሕዝብ ላይ መጨመር የለብንም” ተባባሉ።

ኢትዮጵያ ውላ ካደረች በኋላ የህክምና ማኅበሩ ይደርሳል። መጀመርያ አገር ትኑረን ሲሉ ተማከሩ። ለተግባር ተነሱ፤ የአገር ልጅ ለሚሉት ሁሉ ጥሪ አቀረቡ፣ ደወሉ፣ጻፉ።

ይህ ማኅበር ያን ቀን በቁጭት ተወለደ። ስሙም የኢትዮጵያ እርቅና የሰላም ኅብረት ተባለ።

ዩናይትድ ኪንግደም ተቀምጦ ኢትዮጵያ ሰላም ማምጣት ይቻላል?

ይህ ማኅበር አሁን 50 የሚሆኑ በትምህርታቸው እጅግ የገፉ ምሁራንን አሰባስቧል። ሐኪሞች ብቻ አይደሉም ታዲያ። ሳይንቲስቶች፣ መምህራን፣ የሰርጓጅ መርከብ መሐንዲስ፣ የግጭት አፈታት ከፍተኛ አማካሪዎችን፣የአእምሮ ጤና ባለሙያዎችን፣ የሕጻናት ጤና ስፔሻሊስቶች፣ የቀዶ ጥገናና ንቅለ ተከላ ሐኪሞች ወዘተ. ያቀፈ ማኅበር ነው። የኢትዮጵያ እርቅና የሰላም ኅብረት።

በቅርብ በሎንዶን ደመቅ ያለ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገው ነበር፤ ስለ ኢትዯጵያዊነት የሚል። ብዙዎቹ በአካል የተገናኙት ያኔ ነው። ማኅበሩን ሲመሰርቱ ዓላማ እንጂ ሌላ ጉዳይ አላገናኛቸውም። ኢትዯጵያዊነት ብለው ሲጮኹ ሌላ ማንነትን ደፍጥጠው አልነበረምና ኋላ ላይ የትውልድ ስፍራን እንደነገሩ ሲጠያየቁ ግማሾቹ የትግራይ ልጆች ሆነው ተገኙ፣ ሌሎች ከወለጋ፣ ሌሎች ከሆሳእና፣ ሌሎች ከጎጃም፣ ከወሎ፣ ከአዲስ አበባ… መሆናቸው አስደሰታቸው። አስበውበት ባይሆንም ኅብረ ቀለማምነቱ፣ ጌጥ ሆናቸው እንጂ አላቃቃራቸውም። አገር ምን ማለት እንደሆነ በተግባር አዩት።

ብዙዎቹ አባላት ታዲያ ከ15 እና ከ20 ዓመታት በላይ ከአገራቸው ርቀው ይቆዩ እንጂ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ስለ ኢትዮጵያ መጨነቃቸው አልቀረም፤ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነገሩ እያሰጋቸው የመጣ ይመስላል።

“የትኛውም ኢትዮጵያዊ እኮ እንደው በአካል ከአገሬ ወጣሁ ይበል እንጂ በመንፈስ ኢትዮጵያን ተለይቶ ማደር አይችልም። ይቻለዋል ብለህስ ነው?” ይላሉ ዶ/ር ዓለማየሁ።

እነዚህ በታላቋ ብሪታኒያ የሚኖሩ ምሁራን ብዙዎች ጭንቀታቸውን ውጠው ከዛሬ ነገ ምን ሊመጣ ይሆን በሚል ውጥረት ዝም ባሉበት ወቅት ዝም አንልም ያሉ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል።

ብዙ የድርጊት መርሐ ገብሮችን ነድፈዋል። ስለ ሰላም መስበክ ብቻ ሳይሆን በህዳሴው ግድብ ዙርያ ተሰሚነታቸውን በመጠቀም ለ4 ቀናት የሚዲያ ዘመቻ አድርገው ነበር።

በሰላም ዙርያ በየጊዜው የዲጂታል ጉባኤዎችን ያዘጋጃሉ። ኮቪድ ወረርሽኝ ብዙ የመስክ ሥራ ውስጥ እንዳይገቡ ቢያግዳቸውም ለወገናቸው የሕክምና ቁሳቁስ አሰባስበው አገር ቤት ልከዋል።

የዓለም ሰላም ቀንን አስመልክተው በዌቢናር ትምህርተ ጉባኤ ካቀረቡት ምሁራን መካከል ዶ/ር ፀሐይ አጥላው ይገኙበታል። ዶ/ር ፀሐይ ሥመ ጥር ሳይንቲስት ናቸው። ሴቶች በሰላም ዙርያ ያላቸውን ሚና ያጎሉት ዶ/ር ጸሐይ ለእርቅና ሰላም የሴቶችና እናቶችን ሚና ጉልህ እንደሆነና ይህንኑ ለመልካም ተግባር መጠቀም አስፈላጊነት ላይ አተኩረዋል።

በዚህ ማኅበር ውስጥ ከሚገኙ አመራሮች አንዱ አቶ ወንድሙ ነጋሽ ናቸው። በሙያ ኢንጂነር ይሁኑ እንጂ ይበልጥ የሚታወቁት በአእምሮ ሳይንስ ዘርፍ ተመራማሪነታቸው ነው። “ሁሉም ጦርነቶች የተወለዱት ከሰዎች አእምሮ ነው፣ አእምሮን ካከምን ሌላው ሁሉ ቀላል ነው።” ይላሉ።

አቶ ወንድሙ በተደጋጋሚ ለማኅበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎች በሚያቀርቧቸው ሴሚናሮች ውስጥ ከጥላቻ ንግግር ለመራቅ፣ “እኛና እነሱ” ከሚለው ትርክትና ክፉ አባዜ ለመውጣት፣ የሰውን ክብሩነት በሰውነቱ ብቻ ለመመተር፣ በአጠቃላይ አእምሮን እንዴት ወደ ሰላም መግራት እንደሚቻል ትምህርተ ጉባኤ ያቀርባሉ።

“ሰላም ስለፈለግነው ብቻ አይመጣም፣ ይህን እንረዳለን፣ ፖለቲካ ውስብስብ ነው፣ ይህንንም እንረዳለን። ግን ደግሞ አገር ስትታመም የበይ ተመልካች መሆን አንሻም” ይላሉ የካንሰር ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ዓለማየሁ።

ቢቢሲ አንድ ጥያቄ አንስቶላቸው ነበር ለማኅበሩ ጸሐፊ። “ከባሕር ማዶ ቁጭ ብሎ በአገር ቤት ሰላም ማምጣት የሚመስል ነገር ነው? የሚል። በእርግጥ በኢንተርኔት ሰላም ማምጣት ይቻላል?”

ዶ/ር ዓለማየሁ ለዚህ ምላሻቸው ፈጣን ነው። መጀመርያውኑስ ሰላም የደፈረሰው በኢንተርኔት በመሸጉ የዲጂታል ጦር አበጋዞች አይደለምን? ሲሉ ችግሩም፣ የችግሩ መፍትሄም ከዲጂታሉ ዓለም ጎራ እንደሆነ ያሰምሩበታል።

“ኢትዮጵያ ብዙ አበሳ ያለባት አገር ናት። ለጊዜው ግን ትልቁ ህመሟ ከዲጂታል ዓለም የሚመነጨው የጥላቻ ንግግር ነው።” ይላሉ፣ ደጋግመው።

ምሁራኑ ከትናንትና በስቲያ ዕለት ጀምሮ፣ የዓለም የሰላም ቀንን በሚመለከት የተለያዩ የዌቢናር ውይይቶች እያካሄዱ ሲሆን ለአንድ ሳምንት “የዲጂታል የጦር አውርድ” (Digital ceasefire) ጥሪ አቅርበዋል። ይህ እምብዛምም ያልተሰማ ነገር ነው። ለምን አስፈለገ? ምንስ ማለት ነው?

ጉባኤያተኞችን ለ15 ደቂቃ ሰላማዊና ግጭት አልባ ኢትዮጵያን በሕሊናቸው እንዲያስቡ የጠየቁት የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ይህን መልካም ስሜት ለማቆየት ቢያንስ ለአንድ ሳምንት ኢትዮጵያዊያን የጥላቻ ንግግሮችን በፌስቡክ ከመጻፍ ብቻ ሳይሆን ከማንበብ፣ ከማየትና አስተያየት ከመስጠት እንዲታቀቡ ተማጽነዋል።

ይህም የዓለም የሰላም ቀንን አስመልቶ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ አዲስ ዘመቻ ነው። በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከጥላቻ ንግግሮች ለአንድ ሳምንት በመራቅ እንዴት ጥሩ ስሜት ለራሳቸው መፍጠር እንደሚችሉ እንዲያዩት ይፈልጋሉ፣ ዶ/ር ዓለማየሁ።

ዶ/ር ልዑል ሰገድ አበበ የእርቅና የሰላም ምሁር (በስተግራ)፣ የኢትዮጵያዊያን የእርቅና የሰላም ሕብረት ዋና ጸሐፊ ዶ/ር አለማየሁ ገብረየስ (በስተቀኝ)
 

በማህበራዊ ሚዲያ የደፈረሰ ሰላምን በማህበራዊ ሚዲያም መመለስ ይቻላል?

ዶ/ር ልዑል ሰገድ አበበ የእርቅና የሰላም ጉዳዮች አማካሪ ምሁር ናቸው። የተለያዩ የምርምር ሥራዎቻቸውንም የሰሩት በዚሁ የግጭት አፈታትና እርቀ ሰላም ዙርያ ነው። በታላቋ ብሪታኒያ ብቻም ሳይሆን በምዕራብ አፍሪካ የተለያዩ አገራት ላይ በዚሁ መስክ አገልግለዋል።

ዶ/ር ልዑልሰገድ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን “በሬን የሚያዋልዱ ሰዎች” ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ለማድረግ፣ ማህበራዊ ሚዲያ ከዚህ በተቃራኒ ለሰላምና ሕዝቦችን ለማቀራረብ ሊያገለግል እንደሚችል ይናገራሉ።

የግጭት አንዱ መንስዔ ያልተረጋገጠ መረጃን ማስተላለፍ ነው የሚሉት ምሁሩ፣ ሁላችንም ከእንዲህ ዓይነት ተግባር መቆጠብ እንደሚያስፈልገን ይመክራሉ።

በርግጥ በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ሰላምን ማምጣት ይቻላል የሚለው ላይ መጠነኛ ጥርጣሬ ቢኖራቸውም፣ ሐሰተኛ መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮች ግን እንዲቆሙ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ገልፀዋል።

እነዚያ መረጃዎችና ንግግሮች ቆሙ ማለት ደግሞ ለሰላም የመጀመሪያው በር ተከፈተ ማለት ሊሆን ይችላል ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ይገልፃሉ።

በተጨማሪም ማህበራዊ ሚዲያ አያያዙን ካወቅንበት ሃሳብን ገንቢ በሆነ መልኩ የማቅረብ፣ የመከራከር ባህልን እንድናዳብር ለማድረግ አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላልም ብለው ያምናሉ።

ዶ/ር አለማየሁ ይህን የዶ/ር ልኡልሰገድን ሐሳብ ያጠናክራሉ። “ኢትዮጵያ ብዙ አበሳ ያለባት አገር ናት” ካሉ በኋላ፣ ከዚህ ሁሉ “ክፉኛ ያመማት” ደግሞ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች እና ጥላቻ ንግግሮች ናቸው” ይላሉ።

እንደ እርሳቸው እምነት በዲጂታል ቴክኖሎጂን የተዘራን ክፉ ሃሳብ ማከም የሚቻለው በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ብቻ ነው።

ሰላም በአንድ ቀን ወርክሾፕ የሚገኝ አይደለም የሚሉት ዶ/ር ልኡልሰገድ በበኩላቸው “ሰላም ሂደት” መሆኑን ያሰምሩበታል።

ሂደቱን ለማገዝም የሰዎችን አስተሳሰብና አመለካከት መለወጥ እንደሚያስፈልግ፣ ሰዎች እንዲናገሩ፣ ሃሳባቸውን እንዲገልፁ ቦታና ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚገባ ይናገራሉ።

ግጭትን እንደመቅሰፍት አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ልኡልሰገድ፤ ግጭት መቅሰፍት ሳይሆን የሃሳብ አለመግባባት ወይንም የመረጃዎች አለመጣጣም ነው በማለት እንደነዚህ አይነት ነገሮችን ቁጭ ብሎ በመወያየት መፍታት እንደሚቻል ያስረዳሉ።

ይህ ግጭትን በውይይት የመፍታት ባህል በአገሪቱ በሚገኙ በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ መኖሩን ገልፀው፣ እነዚያን ግጭት መፍቻ ነባር ባህሎች አምጥቶ ለሰላም መጠቀም እንደሚገባ ያስረዳሉ።

“መሣሪያ ዘላቂ ሰላምን አያሰፍንም”

ከአገር በብዙ ማይሎች ርቀው የወገንን ዜና በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን በኩል ሲሰሙ በአካል ተገኝተው ምንም ማድረግ ባይችሉም ፣ ምንም ማድረግ አንችልም ብለው እንደማያስቡ የሚናገሩት ደግሞ ዶ/ር አለማየሁ ናቸው።

” የምንችለውን ያክል እናድርግ” ብለው ለሰላም መምጣት እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ።

ሰላምን በአንድ ሰው የሚመጣ ጉዳይ አይደለም የሚሉት ዶ/ር ልኡልሰገድ፣ “ሰላምን መንግሥት ብቻውን፣ ሊያመጣው የሚችል ጉዳይ አይደለም። ሰላምን ፖሊስ፣ ጦር ሰራዊት ሊያመጣው አይችልም፤ ሁሉም በጋራ ኃላፊነት መስራት ሲችል ነው ሰላም የሚመጣው” ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሰላም ማጣት በየደቂቃው፣ በየሰዓቱ በየእለቱ ያሳስበኛል የሚሉት ዶ/ር አለማየሁ፣ ሰላም ከእጃችን አምልጦ ወደ ቀውስ ውስጥ ከተገባ “ማጣፊያው ከባድ ነው” ሲሉ ይገልፃሉ።

ይህንን ጎረቤት አገራትን መመልከት ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ የተከሰቱ የሰላም መደፍረሶችን በማየት ብቻ እንዴት በቀላሉ ወደ ብጥብጥና አለመረጋጋት መግባት እንደሚቻል ማስተዋል ተገቢ መሆኑን ዶ/ር አለማየሁ ይመክራሉ።

ለዚህም እያንዳንዱ ግለሰብ ዛሬ የሚሰራው ስራ የነገ ሰላም ላይ የሚኖረውን አስተዋጽኦን በማየት በጥንቃቄ መራመድ እንዳለበት ያሳስባሉ።

ዶ/ር ልኡልሰገድ በበኩላቸው እያንዳንዱ ኀብረተሰብ “ግጭት በቃኝ፣ በፍርሃት መቀመጥ በቃኝ፣ ቤተሰቦቼን ለጥይት እዳ አልዳርግም፥ እርሻዬን አርሼ መኖር መቻል እፈልጋለሁ” ማለት አለበት ይላሉ።

ያኔ ወታደሩም፣ መንግሥትም ሊረዳ ይችላል በማለት እዚያ ደረጃ እስካልተደረሰ ድረስ ዘላቂ ሰላም ማስፈን እንደማይቻል ያስረግጣሉ።

መሳሪያ ሰላምን አያሰፍንም የሚሉት ምሁሩ፣ የታጠቀ ኃይል ያነገተው መሳሪያ “ዛሬ ላይ ቢያሳልፈው ነገ ላይ ሊያቆመው አይችልም” ብለዋል።

ሰዎች የሰላም ባለቤት እነርሱ መሆናቸውን ማወቅ እንደሚገባቸውና፣ “ግጭት በቃን” ማለት እንደሚያስፈልጋቸው ይናገራሉ።

የአካባቢ ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ አዛውንቶች፣ የሃይማኖት አባቶች በአካባቢያቸው የሚገኝ የሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውር እንዲቆም ለማድረግ “ከራስ ወዳድነት ወጥቶ ለሌሎች ደህንነት መቆም እንደሚያስፈልጋቸው” ይመክራሉ።

አገራችን ለፖለቲከኞች ወይንም ለአክቲቪስቶች ብቻ መተው ኃላፊነት የጎደለው ነገር ነው የሚሉት ዶ/ር አለማየሁ ደግሞ፣ “አይመለከተኝም ብሎ ለእነዚህ ወገኖች አገርን መተው በአንድ ቀን ከተማ አመድ እንደሚሆን አይተናል” ይላሉ።

ዶ/ር ልኡልሰገድ ሕዝቡ ግጭት በቃኝ ካለ “ሰላምን ማስፈን ረዥም ጊዜ ይወስዳል ብዬ አላምን” በማለት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ለማስፈን በአገር ውስጥ ሆነ ከአገር ውጪ ያሉ ሰዎች ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባቸውና ይህንንም መወጣት ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ።

ዶ/ር አለማየሁ በበኩላቸው ሰላምን ለማምጣት ለወጣቶች የመነጋገርንና የመከራከርን መድረክ ማሳየት፣ የኢትዮጵያዊነትን እሴት በማስተማር በመግራት መስራት ይገባል ይላሉ።

ዶ/ር ልዑል ሰገድም ለልጆቻችን የምንናገራቸው ነገሮች ማስተዋል እንደሚገባ ገልፀው፣ “ከማንነት ባሻገር እኛነታችን እየነገሩ ማስተማር ያስፈልጋል” ብለዋል። አክለውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ቢሆኑ፣ ሃሳብን በሃሳብ መመከትን፣ ተማሪዎቻቸው እንዲያጎለብቱ መስራት እንደሚገባቸው ይመክራሉ።

የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ዓለማየሁ የኢትዮጵያ ነገር አሁንም ያባንናቸዋል። ሰላም ቢደፈርስስ? ወደ እርስ በርስ ቀውስ ብንገባስ? ብለው ያስባሉ። ሰላም በእጃችን ላይ ሳለች ብዙም አታስታውቅም የሚሉት ዶ/ር ዓለማየሁ፣ ከእጅ ላይ ሸርተት ብላ እንደ ብርጭቆ ብትወድቅስ? ብለው ይጨነቃሉ።

ዙሪያዋን በቀበሮ እንደተከበበች በአንዲት አጋዘን የሚመስሏት የዛሬዋን ኢትዮጵያን ሁኔታ እያየን እንዴት ዝም እንላለን ይላሉ።

“ለምን የመን ሊቢያና ሶሪያ እንላለን? አየነው እኮ በኛው፤ ያላየነው ምን አለ? ያልሆነው ምን አለ?” ይላሉ። ያቺ ክፉ ቀን እንዳትመጣ ይጨነቃሉ። ነገር ግን ዳር ሆኜ አልጨነቅም፥ የምችለው እያደረኩ እጨነቃለሁ ነው የሚሉት።

“አገርን ለፖለቲከኛና ለአክቲቪስቶች ጥሎ እንዴት ይታደራል?”

Sources: BBC Amharic

About The Author

Related posts

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *