ዓባይ የዘጋውን ዓባይ ይከፍተዋል

ዓባይ ለኢትዮጵያዊያን ታሪክ ነው የስልጣኔያቸው መገለጫ፣ የታሪካቸው ማውጫ፣ ቅኝታቸውን የተቀኙበት ጥበብ ነው፣ ዓባይ ለኢትዮጵያውያን ሕይወት፣ ነጻነት፣ ማንነት ነው፡፡

ዓባይ ለኢትዮጵያውያን ወንዛቸው ብቻ አይደለም፡፡ የሚታይ ልዩ ክብር፣ ሌሎች የማያዩት ልዩ ሚስጥር፣ ፈጣሪ የሰጣቸው፣ ማንም የማይወስድባቸው ነው፡፡ በየዘመናቱ የተነሱት ኃያላን ነን ባዮች ዓባይን መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያን በድለዋል፡፡ ኃይል አደራጅተው፣ በጀት በጅተው፣ ጦር አዝምተው፣ ዓባይን ለራሳቸው ሊያደርጉ ብዙ ጊዜ ጥረዋል፡፡ ዳሩ አንዱም አልተሳካም፡፡ ሁሉም የህልም እንጀራ ሆኖባቸው ቀረ እንጅ፡፡
ዓባይ የሚናፍቁት፣ በቅርበት የማያገኙት፣ በርቀት የሚሳሱለት፣ በቅርበት የማይደርሱበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ መከራዎችን አሳልፋለች፡፡ የተሸረቡባትን የክፋት ገመዶች በጣጥሳለች፡፡ የዓለም ዓይኖች ሁሉ ዓባይ ላይ አነጣጥረው ኖረዋል፡፡ የማይጠግቡ ሆዶች ዓባይ የቋጠረውን ምግብ ለመብላት አዛግተዋል፡፡ የሚገባቸው ባለቤቶቹ ሆኖ ሳለ የማይገባቸው ሊወስዱት ተመኝተውታል፡፡ ከመመኘትም አልፈው ሞክረውታል፡፡
ዓባይ በሀገሩ ምድር አርፎ ወራጅ ውኃ ብቻ ሳይሆን የእድገት ምንጭ ሊሆን ሲታትር የዓለም ዓይኖች ይባስ ብሎ አፈጠጡ፡፡ እኛ ብቻ እንብላው የሚሉ ሁሉ ተቁነጠነጡ፤ ሲሻቸው ተቆጡ፣ እንዲያም ሲል የሰሚ ያለህ እያሉ ተሽቆጠቆጡ፡፡
ኢትዮጵያዊያንም ለዘመናት ከድነን ያስቀመጥነውን የሞሶብ እንጀራ እንበላለን እንጂ፤ ከሰው ሞሶብ እጃችን አንሰድም፣ ማንንም አንጎዳም፣ እኛም አንጎዳም አሉ፡፡ ብቻን መብላት የለመደ ሆድ ግን የኢትዮጵያውያንን ሀሳብ ሊቀበላቸው አልቻለም፡፡ ዓባይ ከጋራ መንጭቶ፣ በጣና ሐይቅ በዝቶ፣ በጉባ በረሃዎች ተዘርግቶ፣ ሌላ ሐይቅ መስርቶ፣ ሀብት፣ በረከት፣ አንድነት፣ ነጻነት እየሆነ ነው፡፡
ይህ ድንቅ ወንዝ በጉባ የተጀመረው ማደሪያው ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ምን አይነት ጥቅም ይኖረው ይሆን ?
በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና የዓለም አቀፍ ጥናት መምህር እምቢአለ በየነ (ረዳት ፕሮፌሰር ) የሕዳሴ ግድብ የጥቅም ጥናት አሁን ላይ የተጀመረ ሳይሆን ቀደም ባለው ጊዜ ነው ይላሉ፡፡
ዓባይ በጉባ አድሮ ኃይል ሲሰጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ከኩራዝ ያወጣል፤ ጭስ ያደከማትን ኢትዮጵያዊት እናት የዓይን እፎይታ ይሰጣል፡፡ የመብራት አቅርቦት ችግር ሲፈታ በአካባቢው የሚደርሰውን የደን ጭፍጨፋ ያስቆማል፣ ኢትዮጵያ ለምለም እንድትሆን ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡
ዓባይ ምስራቅ አፍሪካን በኢኮኖሚና በመልካም ጉርብትና ለማዋሃድ ከፍተኛ አስተዋፆኦ ያለው ነው ብለዋል፡፡ በዓባይ ማረፊያ ከ50 እስከ 70 የሚደርሱ ደሴቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ የተናገሩት ምሁሩ ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የቱሪዝም መዳረሻና የሥራ እድል መፍጠሪያ ይሆናልም ባይ ናቸው፡፡ በዓባይ ማደሪያ በሚፈጠረው ታላቅ ሐይቅ ኢትዮጵያን በዓሳ ምርት ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለሌሎች ሀገራት የሚጠቅም ሀብት ስላላት ሌሎችን ተጠቃሚ በማድረግ ወዳጅነት መፍጠርም ያስችላል ነው ያሉት፡፡ ለተፋሰሱ ሀገራት የተመጣጠነ ውኃ በማድረስና በትነት ሲባክን የነበረውን ውኃ እንደሚያስቀርም ተናግረዋል፡፡
የሕዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ለጠላቶቿ የሚኖረውን ተጋላጭነት እንደሚቀንሰውም ተናግረዋል፡፡ ይህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሚፈጥረው ትስስር ነው ብለዋል፡፡ ግብጽ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ብቻ ሳትሆን በጠላቶች እንድትታጠር ከፍተኛ የሆነ ሥራ መስራቷን የተናገሩት ምሁሩ የዓባይ መጠናቀቅ የግብጽን ሴራ በማክሰም ሀገራቱ በጥቅም እንዲተሳሰሩ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በውጭም በውስጥም ያላትን ተሰሚነት የሚያሳንሰው የዓባይ ፖለቲካ መሆኑን ያመላከቱት ምሁሩ የሕዳሴው ግድብ ሲጠናቀቅ የዓባይን ፖለቲካ መስመር የሚያስይዝ ነውም ብለዋል፡፡ የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ የግብጽን የኃይል አሰላለፍ እንደሚያስተካክለውና የታችኛው የተፋሰሱን ሀገራት ወደ እውነተኛው ውይይት እንደሚያመጣቸውም ተናግረዋል፡፡
በውጩ ዓለም ናይል ሲባል የሚነሳውን የግብጽን ተሰሚነት በመቀዬር ኢትዮጵያ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደርጋልም ነው ያሉት፡፡ ተሰሚነቱ በቀጣናው፣ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ላይ ከፍ ያለ ይሆናል ብለዋል፡፡ በዓባይ የተዘጋው ወደብ በዓባይ ሊከፈት እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ ዓባይ ወደብ ከማስከፈት ባለፈ ሌላ ጥቅም ይዞ እንደሚመጣ ነው የተናገሩት፡፡ ዓባይ ሰጥቶ ለመቀበል ከፍተኛ እድል እንደሚፈጥርም ምሁሩ አብራርተዋል፡፡
የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ በኢትዮጵያ ላይ ለሚደርሰው የጸጥታ ችግርም መፍትሔ ይዞ እንደሚመጣም ነው ያመላከቱት፡፡ ዓባይ ለኢትዮጵያ የሕይወት ጉዳይ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር እምቢአለ ይሄን መነሻ በማድረግ በዓለም ላይ ከትልልቅ ተቋማት ጋር የሚያስተሳስራትን፣ ተሰሚነቷን ከፍ የሚያደርግላትን ሀብት በጥንቃቄ መጠቀም ይገባልም ብለዋል፡፡
ዓባይ ለኢትዮጵያ ከነዳጅ በላይ ነው፣ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሌላቸውን ያላት ናትም ብለዋል፡፡ ዓባይን መጠቀም ካልተቻለ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ እንደ ሀገር በአንድነት በመቆም የሕዳሴውን ግድብ ለጥቅም ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ዓባይ የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ስለሆነ ከዚህ ቀደም የነበሩት ኢትዮጵያዊያን አሳልፈው አልሰጡም የዚህ ዘመን ትውልድም አሳልፎ እንዳይሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ዓባይ መብራት፣ መስኖ፣ ሐይቅ፣ ዓሳና ሌላም ሆኗል እንድንል የውስጥ ጉዳያችንን በማስተካከል መሥራት አለብን፤ አሁን የመጣው ፈተና ግድቡ በመዘግየቱ ስለሆነ በርብርብ ማጠናቀቅ ይገባልም ብለዋል፡፡
ከአጀንዳ ተቀባይነት ወጥቶ አጀንዳ ሰጪ በመሆን ወዳጅና ጠላትን መለዬት እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡ ኢትዮጵያውያን ለዳግም ዓድዋ ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸውም መክረዋል፡፡ በዓባይ ምክንያት የመጣውን ዘመቻ በጋራ መመከት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
የዓባይ ፖለቲካ የጦዘው የውስጡን መታመም ምክንያት በማድረግ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነ ፕሮጄክት በኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም እና ዕውቀት መሠራቱ የኩራት ምንጭ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር እምቢአለ እንደሚሉት የሕዳሴዉ ግድብ ሲጠናቀቅ የጠብ ምንጭ ይደርቃል፤ የዕድገት ምንጭ ይፈልቃል ፡፡
በታርቆ ክንዴ